ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 3:2-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤

3. እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው።

4. ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስቲ ወደ እኛ ተመልከት” አለው።

5. ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት አስቦ በትኵረት ተመለከታቸው።

6. ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤

7. ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ፤

8. ዘሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ።

9. ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣

10. ይህ ሰው ቀደም ሲል ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ።

11. የተፈወሰውም ለማኝ ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋር ጥብቅ ብሎ አብሮአቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደነበሩበት ‘የሰሎሞን መመላለሻ’ ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 3