ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 25:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ስለዚህ ከባለሥልጣኖቻችሁ መካከል አንዳንዶች ከእኔ ጋር ይምጡና ሰውየው ጥፋት ካለበት ክሱን በዚያው ያቅርቡ።”

6. ከእነርሱም ጋር ስምንት ወይም ዐሥር ቀን ያህል ከሰነበተ በኋላ፣ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በማግስቱም ፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ።

7. ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ፣ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁድ ከበቡት፤ በማስረጃ ያልተደገፉ ብዙ ከባድ ክሶችም አቀረቡበት።

8. ጳውሎስም፣ “እኔ በአይሁድም ሕግ ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሣር ላይ የፈጸምሁት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።

9. ፊስጦስም ለአይሁድ በጎ ለመዋል ፈልጎ፣ ጳውሎስን “ስለዚህ ጒዳይ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ በእኔ ፊት ለመፋረድ ፈቃደኛ ነህን?” አለው።

10. ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “አሁንም ቢሆን ፍትሕ ማግኘት በምችልበት፣ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ፤ አንተ ራስህ በሚገባ እንደምታውቀው በአይሁድ ላይ ምንም በደል አልፈጸምሁም፤

11. ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ በደል ከተገኘብኝ፣ አልሙት አልልም፤ እነዚህ አይሁድ የሚያቀርቡብኝ ክስ እውነት ካልሆነ ግን፣ እኔን ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል የለም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ።”

12. ፊስጦስ ከመማክርቱ ጋር ከተመካከረ በኋላ፣ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልህ፣ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” አለው።

13. ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤

14. በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጒዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤

15. ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከሰውት ነበር።

16. “እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው።

17. ስለዚህ ከሳሾቹ ከእኔ ጋር ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ ጒዳዩን ሳላጓትት በማግስቱ ችሎት ተቀምጬ ያን ሰው እንዲያቀርቡት አዘዝሁ።

18. ከሳሾቹም ተነሥተው በመቆም ሲናገሩ፣ እኔ ያሰብሁትን ያህል ከባድ ክስ አላቀረ ቡበትም፤

19. ይልቁን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ሞቶ ስለ ነበረው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው፣ ስለ ኢየሱስ ይከራከሩት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 25