ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 22:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “ከዚያም ሐናንያ የተባለ ሰው ሊያየኝ ወደ እኔ መጣ፤ እርሱም ሕግን በጥንቃቄ የሚጠብቅና በዚያ በሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ነበረ።

13. በአጠገቤም ቆሞ፣ ‘ወንድም ሳውል ሆይ፤ ዐይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ፤ እኔም በዚያችው ቅጽበት አየሁት።

14. “እርሱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፤ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና ቃሉን ከአንደበቱ እንድትሰማ መርጦሃል፤

15. ስላየኸውና ስለ ሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆነዋለህና።

16. ታዲያ፣ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነሥተህ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ፤ ከኀጢአትህም ታጠብ።’

17. “ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ በቤተ መቅደስ ስጸልይም ተመሰጥሁ፤

18. ጌታም ሲናገረኝ አየሁ፤ እርሱም አሁኑኑ፣ ‘ፈጥነህ ከኢየሩሳሌም ውጣ! ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና’ አለኝ።

19. “እኔም እንዲህ አልሁት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ በአንተ የሚያምኑትን ሰዎች ለማሰርና ለመደብደብ፣ በየምኵራቡ ስዞር እንደ ነበር እነዚህ ሰዎች ያውቃሉ፤

20. ደግሞም የአንተን ሰማዕት የእስጢፋኖስን ደም በሚያፈሱበት ጊዜ፣ በድርጊታቸው ተስማምቼ በቦታው ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ እጠብቅ ነበር።’

21. “ጌታም፣ ‘ሂድ፤ በሩቅ ወዳሉት አሕዛብ እልክሃለሁና’ አለኝ።”

22. ሕዝቡም ይህን ቃል እስኪናገር ድረስ ሰሙት፤ ከዚህ በኋላ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፣ “ይህስ ከምድር ገጽ ይወገድ! በሕይወት መኖር አይገባውም! ብለው ጮኹበት።

23. እነርሱም እየጮኹና ልብሳቸውን እየወረወሩ፣ ትቢያም ወደ ላይ እየበተኑ ሳሉ፣

24. የጦር አዛዡ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈር እንዲያስገቡትና ሕዝቡ ለምን እንዲህ እንደሚጮኹበት እየተገረፈ እንዲመረመር ትእዛዝ ሰጠ።

25. ጳውሎስም በጠፍር ወጥረው ሊገርፉት ሲሉ፣ አጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፣ “አንድን የሮም ዜጋ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋልን?” አለው።

26. የመቶ አለቃውም ይህን ሲሰማ፣ ወደ ጦር አዛዡ ቀርቦ፣ “ምን እያደረግህ እንደሆነ ዐውቀሃል? ሰውየው እኮ ሮማዊ ነው” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 22