ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 21:28-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. እንዲህም እያሉ ጮኹ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን እንዲሁም ይህን ስፍራ በማጥላላት በደረሰበት ስፍራ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ከዚህም በላይ ግሪኮችን ወደ ቤተ መቅደስ እያስገባ ይህን የተቀደሰ ስፍራ የሚያረክሰው እርሱ ነው።”

29. ይህንም ያሉት ቀደም ሲል፣ የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማው ውስጥ ስላዩት፣ ጳውሎስ እርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ ይዞ የገባ ስለ መሰላቸው ነበር።

30. ከተማው በሙሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ከየአቅጣጫው እየተሯሯጡ መጡ፤ ጳውሎስንም ይዘው እየጐተቱት ከቤተ መቅደሱ ግቢ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያውኑ ተዘጉ።

31. ሊገድሉት ሲፈልጉም የኢየሩሳሌም ከተማ ፍጹም ታወከች፤ ወሬውም ለሮማ ጦር አዛዥ ደረሰው።

32. እርሱም ወዲያው አንዳንድ የጦር መኰንኖችንና ወታደሮችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም መኰንኖቹንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ።

33. የጦር አዛዡም ቀርቦ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ጠየቀ።

34. ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ።

35. ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው።

36. ከኋላ የተከተለውም ሕዝብ፣ “አስወግደው!” እያለ ይጮኽ ነበር።

37. ወታደሮቹ ወደ ጦር ሰፈር ይዘውት ሊሄዱ ሲሉ፣ ጳውሎስ ጦር አዛዡን፣ “አንድ ነገር እንድነግርህ ፍቀድልኝ?” አለው።አዛዡም እንዲህ አለው፤ “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህ?

38. አንተ ከዚህ ቀደም ዐመፅ አስነሥተህ፣ አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮችን ወደ በረሓ ያሸፈትኸው ግብፃዊ አይደለህምን?”

39. ጳውሎስም፣ “እኔስ በኪልቅያ ያለችው የታዋቂዋ የጠርሴስ ከተማ ነዋሪ የሆንሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ ለሕዝቡ ንግግር እንዳደርግ ፍቀድልኝ” አለው።

40. ጳውሎስም የጦር አዛዡን ካስፈቀደ በኋላ፣ በደረጃው ላይ ቆሞ ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ ሁሉም ጸጥ ባሉ ጊዜ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ አለ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 21