ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 20:21-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም አጥብቄ መስክሬላቸዋለሁ።

22. “አሁንም እዚያ ስደርስ የሚደርስብኝን ባላውቅም፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንድሄድ ግድ እያለኝ ነው።

23. ነገር ግን በምሄድባቸው ከተሞች ሁሉ እስራትና መከራ እንደሚጠብቀኝ መንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል።

24. ይሁን እንጂ ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት።

25. “አሁንም ቢሆን፣ በመካከላችሁ ተዘዋውሬ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ፣ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲያ ፊቴን እንደማታዩ ዐውቃለሁ።

26. ስለዚህ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆኔን በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ፤

27. የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽ የተቈጠብሁበት ጊዜ የለምና።

28. ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።

29. እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ።

30. ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ።

31. ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን ምንም ያህል ሳላቋርጥ በእንባ እያንዳንዳችሁን እንደ መከርኋችሁ አስታውሱ።

32. “አሁንም ለእግዚአብሔር፣ እንዲሁም ሊያንጻችሁና በቅዱሳኑ ሁሉ መካከል ርስት ሊያወርሳችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል ዐደራ እሰጣችኋለሁ።

33. የማንንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤

34. እነዚህ እጆቼ ለእኔና ከኔ ጋር ላሉት በሚያስፈልገን ነገር እንዳገለገሉን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

35. በጒልበታችን ደክመን ችግረኞችን መርዳት እንዳለብን ባደረግሁት ሁሉ አሳይቻችኋለሁ፤ ‘ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው’ ያለውን የጌታ የኢየሱስን ቃል እናስታውስ።”

36. ይህን ካለ በኋላ፣ ተንበርክኮ ከሁሉም ጋር ጸለየ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 20