ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 18:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. በየሰንበቱም ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ጋር በምኵራብ ውስጥ እየተነጋገረ ሊያሳምናቸው ይጥር ነበር።

5. ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስ በስብከት እየተጋ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለአይሁድ ይመሰክር ነበር።

6. ነገር ግን በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፣ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን! እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።

7. ከዚያም ወጥቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደተባለ፣ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህም ሰው ቤት በምኵራቡ አጠገብ ነበር።

8. የምኵራብ አለቃ የነበረው ቀርስጶስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ጳውሎስ ሲናገር የሰሙ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ተጠመቁ።

9. ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ ተናገር፣ ዝምም አትበል፤

10. እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ማንም በአንተ ላይ ተነሥቶ ሊጐዳህ አይችልም፤ በዚች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።”

11. ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማራቸው አንድ ዓመት ተኩል አብሮአቸው ተቀመጠ።

12. ጋልዮስ የአካይያ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም፣

13. “ይህ ሰው ሕጉ በማይፈቅደው መንገድ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ እያሳሳታቸው ነው” አሉ።

14. ጳውሎስ ሊናገር ገና አፉን ሲከፍት፣ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፤ “የአይሁድ ሰዎች ሆይ፤ ያቀረባችሁት ጒዳይ ስለ ዐመፅ ወይም ስለ ከባድ ወንጀል ቢሆን ኖሮ ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር፤

15. ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 18