ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 16:2-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው።

3. ጳውሎስም ይህ ሰው ከእርሱ ጋር እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ አባት የግሪክ ሰው እንደሆነ ያውቁ ነበርና።

4. እነርሱም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን ውሳኔ ተቀብለው እንዲጠብቁ ለምእመናኑ ይሰጡ ነበር።

5. አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር።

6. ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ።

7. ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም፤

8. ስለዚህ በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ።

9. ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ።

10. ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።

11. ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጒዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጒዞአችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤

12. ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን።

13. በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 16