ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 12:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የእርሱ መልአክ ነው” አሉ።

16. ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።

17. እርሱም ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ፣ ጌታ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው አስረዳቸው፣ “ስለ ሁኔታው ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሯቸው” አላቸው፤ ከዚያም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።

18. በማግስቱም ጠዋት ወታደሮቹ፣ “ጴጥሮስ የት ገባ?” እያሉ በመካከላቸው ትልቅ ትርምስ ተፈጠረ።

19. ሄሮድስም ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ፣ ዘብ ጠባቂዎቹን በጥብቅ ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ።ከዚያም ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ እዚያ ተቀመጠ።

20. እርሱም ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎች ጋር ጥለኛ ነበር፤ አገራቸው ምግብ የሚያገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለ ነበር፣ የንጉሡን ባለሟል የብላስጦስን ድጋፍ ካገኙ በኋላ፣ አንድ ላይ ሆነው ከንጉሡ ጋር ለመታረቅ ጠየቁ።

21. በቀጠሮውም ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም ንግግር አደረገ።

22. ሕዝቡም፣ “ይህስ የአምላክ ድምፅ እንጂ የሰው አይደለም” ብለው ጮኹ።

23. ሄሮድስም ለእግዚአብሔር ክብር ስላልሰጠ የጌታ መልአክ ወዲያው መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ።

24. የእግዚአብሔር ቃል ግን እያደገና እየሰፋ ሄደ።

25. በርናባስና ሳውልም ተልእኮአቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 12