ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 10:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤

8. የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

9. የተላኩትም ሰዎች በማግስቱ ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ።

10. በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤

11. ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ።

12. በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበሩ አዕዋፍ ነበሩበት።

13. በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።

14. ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኵስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ።

15. ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኵስ አትቍጠረው” አለው።

16. ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨር ቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 10