ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 10:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጒም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤

18. ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ።

19. ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤

20. ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለ ሆንሁ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።”

21. ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጒዳይ ምንድን ነው?” አላቸው።

22. ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት።

23. ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው።ጴጥሮስም በማግስቱ ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ፤

24. በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር።

25. ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት።

26. ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንዳንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው።

27. ጴጥሮስም እያነጋገረው አብሮት ሲገባ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤

28. እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋር እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኵስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 10