ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 10:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በቂሳርያ፣ ‘የኢጣሊያ ክፍለ ጦር’ በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።

2. እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር።

3. አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ።

4. ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው።መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት አርጎልሃል።

5. አሁንም ሰዎች ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤

6. እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፎአል።”

7. ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤

8. የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

9. የተላኩትም ሰዎች በማግስቱ ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ።

10. በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤

11. ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ።

12. በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበሩ አዕዋፍ ነበሩበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 10