ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 9:37-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

37. በማግሥቱ ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው።

38. በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ።

39. መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ አረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጒዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤

40. ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።”

41. ኢየሱስም “እምነት የለሽ ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? በል ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።

42. ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው።

43. ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ።እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣

44. “ይህን የምነግራችሁን ነገር ከቶ እንዳትዘነጉ፤ የሰው ልጅ አልፎ በሰዎች እጅ ይሰጣልና” አለ።

45. እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

46. ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ።

47. ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤

48. እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።”

49. ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለ ማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው።

50. ኢየሱስም፣ አትከልክሉት “የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋር ነውና” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 9