ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 9:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል።

25. ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው?

26. ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።

27. እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።”

28. ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ።

29. በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ።

30. እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤

31. በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር።

32. ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኖአቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ።

33. ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር።

34. ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 9