ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 8:2-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣

3. የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።

4. ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤

5. “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር፤ ወደቀ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት።

6. አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ።

7. ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና አንቆ አስቀረው።

8. ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍም አፈራ።”ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።

9. ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጒም ጠየቁት።

10. እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’

11. “እንግዲህ የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው።

12. በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው።

13. በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው።

14. በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው አድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም።

15. በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።

16. “መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።

17. የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና።

18. እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”

19. ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም።

20. በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 8