ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 6:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር።

2. ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።

3. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን?

4. ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኀብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።”

5. ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

6. በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ።

7. ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር።

8. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካካል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

9. ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።

10. ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 6