ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 23:8-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ሄሮድስም ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ሊያየው ይፈልግ ስለ ነበር፣ ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ታምራት ሲሠራ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር።

9. ብዙ ጥያቄዎችንም አቀረበለት፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰለትም።

10. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው በብርቱ ይወነጅሉት ነበር።

11. ሄሮድስም ከወታደሮቹ ጋር ናቀው፤ አፌዙበትም፤ የክብር ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው።

12. ሄሮድስና ጲላጦስም በዚሁ ዕለት ተወዳጁ፤ ቀደም ሲል ግን በመካከላቸው ጥል ነበረ።

13. ጲላጦስም የካህናት አለቆችን፣ ገዥዎችንና ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቦ፣

14. እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ሕዝቡን ለዐመፅ ያነሣሣል ብላችሁ ወደ እኔ አምጥታችሁት ነበር፤ እኔም በእናንተው ፊት መርምሬው፣ ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም።

15. ደግሞም ሄሮድስ እንዲሁ ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ እንደምታዩት ይህ ሰው ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም፤

16. ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ።”

17. ይህን ያለው በበዓሉ አንድ እስረኛ እንዲፈታላቸው የግድ ያስፈልግ ስለ ነበረ ነው።

18. ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ፣ “ይህን ሰው ወዲያ አስወግደው! በርባንን ፍታልን!” እያሉ ጮኹ፤

19. በርባንም በከተማ ውስጥ የሕዝብ ዐመፅ በማነሣሣትና በነፍስ ግድያ የታሰረ ሰው ነበር።

20. ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ስለ ፈለገ፣ እንደ ገና ተናገራቸው፤

21. እነርሱ ግን፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮኹ ነበር።

22. ጲላጦስም ሦስተኛ ጊዜ፣ “ለምን? ይህ ሰው ምን የፈጸመው ወንጀል አለ? እኔ ለሞት የሚያበቃ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ስለዚህ ቀጥቼ እፈታዋለሁ” አላቸው።

23. እነርሱ ግን ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲሰቀል አጥብቀው ለመኑት፤ ጩኸታቸውም በረታ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 23