ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 23:41-56 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

41. እኛ ላደረግነው ነገር ቅጣት እየተቀበልን ስለ ሆነ፣ ተገቢ ፍርድ ላይ ነን፤ ይህ ሰው ግን አንዳች ክፉ ነገር አላደረገም።”

42. ደግሞም፣ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው።

43. ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው።

44. ጊዜው ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፤

45. የፀሓይ ብርሃን ተከልክሎአልና። የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ተቀዶ ለሁለት ተከፈለ።

46. ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ፤ ይህንም ብሎ ሞተ።

47. የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ጻድቅ ነበር” ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ።

48. ይህንኑ ለማየት በስፍራው ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችም ሁሉ የሆነውን ነገር በተመለከቱ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ።

49. ነገር ግን ኢየሱስን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ እንዲሁም ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች ይህን እየተመለከቱ ከሩቅ ቆመው ነበር።

50. የአይሁድ ሸንጎ አባል የሆነ፣ አንድ ዮሴፍ የሚባል በጎና ጻድቅ ሰው ነበር።

51. ይህ ሰው በሸንጎው ምክርና ድርጊት አልተባበረም ነበረ፣ እርሱም አርማትያስ የምትባል የአይሁድ ከተማ ሰው ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት ይጠባበቅ ነበር።

52. ይህም ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው፤

53. በተፈቀደለትም ጊዜ፣ ሥጋውን አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ከድንጋይ ተፈልፍሎ በተሠራና ገና ማንም ባልተቀበረበት መቃብር ውስጥ አስቀመጠው።

54. ዕለቱ የመዘጋጃ ቀን ነበረ፤ ሰንበትም ሊገባ ነበር።

55. ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋር የመጡት ሴቶችም ተከትለው መቃብሩን አዩ፤ ሥጋውንም እንዴት እንዳስቀመጡት ተመለከቱ።

56. ከዚያም ተመልሰው ሽቱና ቅባት አዘጋጁ፤ ሕጉ በሚያዘው መሠረት በሰንበት ቀን ዐረፉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 23