ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 23:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።ኢየሱስም፣ “አንተውኮ አልህ” አለው።

4. ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፣ “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አለ።

5. እነርሱ ግን፣ “ይህ ሰው ከገሊላ ጀምሮ እዚህ ድረስ መላውን ይሁዳ ሳይቀር እያወከ ነው” እያሉ አጽንተው ተናገሩ።

6. ጲላጦስም ይህን ሲሰማ፣ ሰውየው የገሊላ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ጠየቀ፤

7. ኢየሱስ ከሄድሮስ ግዛት የመጣ መሆኑን ጲላጦስ ባወቀ ጊዜ፣ ሄሮድስ በዚያን ወቅት በኢየሩሳሌም ስለ ነበረ ወደ እርሱ ላከው።

8. ሄሮድስም ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ሊያየው ይፈልግ ስለ ነበር፣ ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ስለ እርሱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ ታምራት ሲሠራ ለማየት ተስፋ ያደርግ ነበር።

9. ብዙ ጥያቄዎችንም አቀረበለት፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰለትም።

10. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም እዚያው ቆመው በብርቱ ይወነጅሉት ነበር።

11. ሄሮድስም ከወታደሮቹ ጋር ናቀው፤ አፌዙበትም፤ የክብር ልብስ አልብሶም ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው።

12. ሄሮድስና ጲላጦስም በዚሁ ዕለት ተወዳጁ፤ ቀደም ሲል ግን በመካከላቸው ጥል ነበረ።

13. ጲላጦስም የካህናት አለቆችን፣ ገዥዎችንና ሕዝቡን በአንድነት ሰብስቦ፣

14. እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ሰው ሕዝቡን ለዐመፅ ያነሣሣል ብላችሁ ወደ እኔ አምጥታችሁት ነበር፤ እኔም በእናንተው ፊት መርምሬው፣ ባቀረባችሁበት ክስ አንዳች ወንጀል አላገኘሁበትም።

15. ደግሞም ሄሮድስ እንዲሁ ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ እንደምታዩት ይህ ሰው ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር አልፈጸመም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 23