ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 22:44-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

44. እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።

45. ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣

46. “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው።

47. እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ።

48. ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።

49. በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት።

50. ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።

51. ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳሶ ፈወሰው።

52. ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን?

53. በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”

54. ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 22