ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 22:27-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

27. ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው።

28. እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤

29. አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤

30. ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድት ጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድ ትፈርዱ ነው።”

31. ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤

32. እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”

33. ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው።

34. ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።

35. ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።

36. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ።

37. እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሶአል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 22