ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 22:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚህ ጊዜ ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር።

2. የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያስወግዱት መንገድ ይፈልጉ ነበር።

3. ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በተቈጠረው የአስቆሮቱ ይሁዳ በተባለው ገባበት፤

4. ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተነጋገረ።

5. እነርሱም በዚህ ደስ ተሰኝተው፣ ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ።

6. እርሱም በነገሩ ተስማማ፤ አሳልፎ ሊሰጣቸውም ሕዝብ የማይገኝበትን ምቹ ጊዜ ይጠብቅ ጀመር።

7. ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ።

8. ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።

9. እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት።

10. እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤

11. ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት።

12. እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”

13. እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 22