ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 20:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ፤

2. እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ለመሆኑ እርሱ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

3. እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስቲ መልሱልኝ፤

4. የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?”

5. እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤

6. ‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለ ሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።”

7. ስለዚህ፣ “ከየት እንደሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት።

8. ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

9. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ።

10. በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት አገልጋዩን ወደ እነዚህ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት።

11. ቀጥሎም ሌላ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት።

12. አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቊስለው ወደ ውጭ ጣሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 20