ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 16:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሀብታም ሰው አንድ መጋቢ ነበረው፤ ይኸው መጋቢ የሀብታሙን ሰው ንብረት እንደሚያባክን ለዚሁ ሀብታም ሰው ወሬ ደረሰው።

2. ስለዚህ አስጠራውና፣ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድን ነው? ከእንግዲህ አንተ መጋቢ ልትሆነኝ ስለማትችል፣ የምታስተዳድረውን ንብረት መቈጣጠሪያ ሒሳብ አስረክበኝ’ አለው።

3. “መጋቢውም በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ከመጋቢነት ሊሽረኝ ነው፤ ለማረስ ጒልበት የለኝም፤ መለመን ደግሞ ዐፍራለሁ፤ ስለዚህ ምን ላድርግ?

4. ከመጋቢነት የተሻርሁ እንደሆነ ሰዎች በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን ዐውቃለሁ።’

5. “ስለዚህ የጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች እያንዳንዳቸውን ጠራ፤ የመጀመሪያውንም ሰው ‘የጌታዬ ዕዳ ምን ያህል አለብህ?’ አለው።

6. “እርሱም፣ ‘አንድ መቶ ማድጋ ዘይት አለብኝ’ አለ። “መጋቢውም፣ ‘የውል ወረቀትህን እንካ፤ ቶሎ ተቀምጠህ “አምሳ ማድጋ” ብለህ ጻፍ’ አለው።

7. “ከዚያም ሌላውን፣ ‘አንተስ ስንት አለብህ?’ አለው። “እርሱም፣ ‘አምሳ ዳውላ ስንዴ’ አለው። “መጋቢውም፣ ‘የብድር ደብዳቤህን እንካ፤ “አርባ ዳውላ” ብለህ ጻፍ’ አለው።

8. “ጌታውም አጭበርባሪውን መጋቢ በብልኅነቱ አደነቀው፤ የዚህ ዓለም ልጆች ከመሰሎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ከብርሃን ልጆች ይልቅ ብልኆች ናቸውና።

9. ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የዚህ ዓለም ገንዘብ ባለቀ ጊዜ በዘላለም ቤት ተቀባይነት እንዲኖራችሁ፣ በዚሁ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አፍሩበት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 16