ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 14:10-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ዝቅተኛውን ስፍራ አይተህ ተቀመጥ፤ ጋባዥህም ሲመጣ፣ ወዳጄ ሆይ፤ ወደ ላይ ከፍ በል ይልሃል፤ አንተም በዚያን ጊዜ አብረውህ በማእድ በተቀመጡ ሰዎች ሁሉ ፊት ትከበራለህ።

11. ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።”

12. ኢየሱስም የጋበዘውን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በአጸፋው እንዳይጋ ብዙህና ብድራትን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጐረቤቶችህን አትጋብዝ።

13. ነገር ግን ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስወሮችን ጥራ፤

14. ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።”

15. ከኢየሱስ ጋር በማእድ ከተቀመጡት መካከል አንዱ ይህን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦ ከማእድ የሚበላ ብፁዕ ነው” አለው።

16. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰው ጠራ፤

17. የግብዣውም ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን እንግዶች፣ እነሆ፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶአልና ኑ ብሎ እንዲጠራ አገልጋዩን ላከባቸው።

18. “ነገር ግን ሁሉም የየራሳቸውን ምክንያት ይፈጥሩ ጀመር፤ አንደኛው፣ ‘ገና አሁን መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ እባክህ፣ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው።

19. “ሌላኛውም፣ ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ እነርሱን ልፈትናቸው ስለ ሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ።

20. “ሌላው ደግሞ፣ ‘ገና ሙሽራ ስለ ሆንሁ ልመጣ አልችልም’ አለ።

21. “አገልጋዩም ተመልሶ መጥቶ ይህንኑ ለጌታው ነገረው። በዚህን ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው አውራ ጐዳናዎችና መተላለፊያ መንገዶች ውጣ፤ ድኾችንና አካለ ስንኩሎችን፣ ዐይነ ስውሮችንና ዐንካሶችን ወደዚህ አስገባቸው’ አለው።

22. “አገልጋዩም፣ ‘ጌታዬ፤ ያዘዝኸው ሁሉ ተፈጽሟል፤ ገና አሁንም ቦታ አለ’ አለው።

23. “ጌታውም አገልጋዩን፣ ‘ወደ ጐዳናዎችና ወደ ገጠር መንገዶች ውጣ፤ ቤቴም እንዲሞላ ያገኘኸውን ሁሉ በግድ አምጥተህ አስገባ፤

24. እላችኋለሁና ከተጋበዙት ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንድ ሰው እንኳ ግብ ዣዬን አይቀምስም አለው።’ ”

25. ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዙ ሳለ፣ ኢየሱስ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 14