ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 12:48-59 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

48. ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል።

49. “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፤ አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ!

50. ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እስኪፈጸምም ድረስ እንዴት ተጨንቄአለሁ?

51. በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው።

52. ከአሁን ጀምሮ እርስ በርስ የተለያዩ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ አምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሁለቱ በሦስቱ ላይ፣ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ፤

53. አባት በወንድ ልጁ ላይ፣ ወንድ ልጅም በአባቱ ላይ፣ እናት በሴት ልጇ ላይ፣ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ፣ አማት በምራቷ ላይ፣ ምራትም በአማቷ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።”

54. ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ዝናብ ሊመጣ ነው ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤

55. የደቡብ ነፋስም ከደቡብ በኩል ሲነፍስ፣ ቀኑ ሞቃት ይሆናል ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል።

56. እናንት ግብዞች፤ የምድሩንና የሰማዩን መልክ መመርመር ታውቁበታላችሁ፤ ታዲያ ይህን የአሁኑን ዘመን መመርመር እንዴት ተሳናችሁ?

57. “ታዲያ ራሳችሁ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለምን አትፈርዱም?

58. ከባላጋራህ ጋር ወደ ዳኛ ፊት ለመቅረብ ስትሄድ፣ ገና በመንገድ ላይ ሳለህ ለመታረቅ ጥረት አድርግ፤ አለበለዚያ ጐትቶ ወደ ዳኛው ይወስድሃል፤ ዳኛውም ለመኰንኑ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ መኰንኑም ወደ ወህኒ ይጥልሃል፤

59. እልሃለሁ፤ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 12