ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 12:37-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

37. ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል።

38. ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው።

39. ይህን ግን ዕወቁ፤ ሌባ በምን ሰዓት እንደሚመጣ የቤቱ ባለቤት ቢያውቅ ኖሮ፣ ቤቱ ሲቈፈር ዝም ብሎ ባላየ ነበር።

40. እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤ የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣልና።”

41. ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነው ወይስ ለሁሉም ጭምር ነው?” አለው።

42. ጌታም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እንግዲህ፣ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልህ መጋቢ ማነው?

43. ጌታው ሲመለስ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው አገልጋይ እርሱ ብፁዕ ነው።

44. እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ይሾመዋል።

45. ዳሩ ግን ያ አገልጋይ፣ ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል፤ ብሎ ቢያስብና ወንድና ሴት አገልጋዮችን ቢደበድብ፣ ደግሞም እንዳሻው መብላት፣ መጠጣትና መስከር ቢጀምር፣

46. የዚያ አገልጋይ ጌታ ባላሰበው ቀንና ባልጠረጠረው ሰዓት ይመጣበታል፤ ስለዚህ ይቈራርጠዋል፤ ዕድል ፈንታውንም ከማያምኑ ጋር ያደርጋል።

47. “የጌታውን ፍላጎት እያወቀ የማይዘጋጅና ፈቃዱን የማያደርግ አገልጋይ እርሱ ክፉኛ ይገረፋል፤

48. ነገር ግን ይህን ሳያውቅ ቀርቶ መገረፍ የሚገባውን ያህል ያደረገ አገልጋይ በጥቂቱ ይገረፋል። ብዙ ከተሰጠው ሁሉ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተቀበለም ብዙ ይጠበቅበታል።

49. “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኰስ ነው፤ አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ!

50. ነገር ግን የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እስኪፈጸምም ድረስ እንዴት ተጨንቄአለሁ?

51. በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ ይመስላችኋል? አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው።

52. ከአሁን ጀምሮ እርስ በርስ የተለያዩ በአንድ ቤተ ሰብ ውስጥ አምስት ሰዎች ይኖራሉ፤ ሁለቱ በሦስቱ ላይ፣ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ፤

53. አባት በወንድ ልጁ ላይ፣ ወንድ ልጅም በአባቱ ላይ፣ እናት በሴት ልጇ ላይ፣ ሴት ልጅም በእናቷ ላይ፣ አማት በምራቷ ላይ፣ ምራትም በአማቷ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ።”

54. ደግሞም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ደመና በምዕራብ በኩል ሲወጣ ስታዩ ወዲያው፣ ዝናብ ሊመጣ ነው ትላላችሁ፤ እንደዚያም ይሆናል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 12