ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 12:12-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በዚያ ሰዓት መንፈስ ቅዱስ መናገር የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና።”

13. ከሕዝቡም መካከል አንድ ሰው፣ “መምህር ሆይ፤ ወንድሜ ውርስ እንዲያካፍለኝ ንገረው” አለው።

14. ኢየሱስም፣ “አንተ ሰው፤ በእናንተ ላይ ፈራጅ ወይም ዳኛ ያደረገኝ ማነው?” አለው።

15. ደግሞም፣ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግ ብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ” አላ ቸው።

16. ቀጥሎም እንዲህ ሲል ምሳሌ ነገራቸው፤ “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤

17. ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ።

18. “እንዲህም አለ፤ ‘እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤

19. ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’

20. “እግዚአብሔር ግን፣ ‘አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊውስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?’ አለው።

21. “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”

22. ከዚያም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፤ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ሕይወታችሁ ምን እንደምትበሉ፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤

23. ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና።

24. ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን?

25. ለመሆኑ፣ ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማነው?

26. እንግዲህ ቀላሉን ነገር እንኳ ማድረግ የማትችሉ ከሆነ፣ ስለ ሌላው ነገር ለምን ትጨነቃላችሁ?

27. “እስቲ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም።

28. እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 12