ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 12:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያን ጊዜ፣ በብዙ ሺህ የሚቈጠር ሕዝብ እርስ በርስ እስኪረጋገጥ ድረስ ተሰብስቦ ሳለ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ ይህም ግብዝነት ነው።

2. የማይገለጥ የተሸፈነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም።

3. ስለዚህ በጨለማ ያወራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ ያንሾካሾካችሁት በሰገነት በይፋ ይነገራል።

4. “ወዳጆቼ ሆይ፤ እላችኋለሁ ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ።

5. ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፤ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ።

6. አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም።

7. የእናንተ የራሳችሁ ጠጒር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።

8. “እላችኋለሁ፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል።

9. በሰው ፊት የሚክደኝም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል።

10. በሰው ልጅ ላይ የማቃለል ቃል የሚሰነዝር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ግን አይሰረይለትም።

11. “ሰዎች ይዘው ወደ ምኵራብ፣ ወደ ገዥዎችና ወደ ባለ ሥልጣናት ባቀረቧችሁ ጊዜ፣ እንዴት ወይም ምን እንደምትመልሱ አትጨነቁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 12