ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 11:25-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ሲመለስም ቤቱ ተጠራር ጐና ተስተካክሎ ያገኘዋል።

26. ከዚያም በኋላ ሄዶ ሌሎች ከእርሱ የከፉ ሰባት አጋንንት ይዞ ይመጣል፤ ገብተውበትም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያ ሰው ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታ የከፋ ይሆንበታል።

27. ኢየሱስ ይህን እየተናገረ እያለ፣ ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፣ “የተሸከመችህ ማሕፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው” አለችው።

28. እርሱ ግን፣ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” አለ።

29. ብዙ ሕዝብ እየተሰበሰበ በሄደ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ታምራዊ ምልክት ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ አይሰጠውም።

30. ምክንያቱም ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደሆናቸው የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል።

31. የደቡቧ ንግሥት በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ እርሷ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና፤ እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

32. የነነዌ ሰዎችም በፍርድ ጊዜ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ የዮናስን ስብከት ሰምተው ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆ፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

33. “መብራት አብርቶ በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁን የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል።

34. የሰውነትህ ብርሃን ዐይንህ ናት፤ ዐይንህ ጤናማ ስትሆን መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ታማሚ ከሆነች ግን መላ ሰውነትህ የጨለመ ይሆናል።

35. ስለዚህ በውስጥህ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተጠንቀቅ።

36. እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ከሆነና የጨለመ የሰውነት ክፍል ከሌለበት፣ የሰውነትህ ሁለንተና መብራት በወገግታው ያበራልህ ያህል ይደምቃል።”

37. ኢየሱስ ንግግሩን እንደ ጨረሰ፣ አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምግብ እንዲበላ ጋበዘው፤ እርሱም አብሮት ገብቶ በማእድ ተቀመጠ።

38. ፈሪሳዊውም ኢየሱስ ከምግብ በፊት እጁን እንዳልታጠበ ባየ ጊዜ ተደነቀ።

39. ጌታም እንዲህ አለው፤ “አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጫዊ ክፍል ታጸዳላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በስስትና በክፋት የተሞላ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 11