ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 11:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?

13. እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”

14. አንድ ቀን ኢየሱስ ድዳ ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣለት በኋላ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም ተገረመ።

15. አንዳንዶቹ ግን፣ “በአጋንንት አለቃ፣ በብዔልዜቡል፣ አጋንንትን ያወጣል” አሉ፤

16. አንዳንዶቹ ደግሞ ሊፈታተኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ከእርሱ ይፈልጉ ነበር።

17. ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ የሚለያይ ቤትም ይወድቃል።

18. ሰይጣንም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ፣ መንግሥቱ እንዴት ይጸናል? አጋንንትን በብዔልዜቡል እንደማወጣ ትናገራላችሁና።

19. እንግዲህ እኔ አጋንንትን የማወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ በማን ያወጧቸው ይሆን? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።

20. እኔ ግን አጋንንትን የማወጣው በእግዚአብሔር ጣት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ መጣች ዕወቁ።

21. “ብርቱ ሰው በሚገባ ታጥቆ ቤቱን ከጠበቀ፣ ንብረቱ በሰላም ይቀመጣል።

22. ነገር ግን ይበልጥ ብርቱ የሆነ ሰው መጥቶ ካጠቃውና ካሸነፈው ታምኖበት የነበረውን ትጥቁን ያስፈታዋል፤ ምርኮውንም ወስዶ ለሌሎች ያካፍላል።

23. “ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ይበትናል።

24. “ርኵስ መንፈስ ከሰው ሲወጣ ዕረፍት ፍለጋ ውሃ በሌለበት ስፍራ ይንከራተታል፤ ሳያገኝም ሲቀር፣ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 11