ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 1:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ።

13. መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።

14. በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤

15. በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል።

16. ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤

17. የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።”

18. ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው።

19. መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤

20. እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።”

21. በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር።

22. ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ።

23. ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

24. ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤

25. እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።

26. በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤

27. የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 1