ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጢሞቴዎስ 4:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።

7. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።

8. ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

9. በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤

10. ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዶአልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤

11. ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና።

12. ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ።

13. ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖስ፣ ጥቅልል መጻሕፍቱን በተለይም የብራና መጻሕፍቱን አምጣልኝ።

14. አንጥረኛው እስክንድሮስ ብዙ ጒዳት አድርሶብኛል፤ ጌታ ግን የእጁን ይሰጠዋል።

15. መልእክታችንን እጅግ ተቃውሞአልና፣ አንተም ከእርሱ ተጠንቀቅ።

16. በተከሰስሁበት ነገር የመጀመሪያ መከላከያዬን ሳቀርብ ማንም ሊያግዘኝ አልመጣም፤ ነገር ግን ሁሉ ትተውኝ ሄዱ። ይህንም አይቍጠርባቸው።

17. ነገር ግን መልእክቱ በእኔ አማካይነት በሙላት እንዲሰበክና አሕዛብ ሁሉ እንዲሰሙት ጌታ በአጠገቤ ቆሞ አበረታኝ፤ ከአንበሳም መንጋጋ አዳነኝ።

18. ጌታ ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል፤ ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል፤ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።

19. ለጵርስቅላና ለአቂላ፣ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ጢሞቴዎስ 4