ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጢሞቴዎስ 4:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤

2. ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።

3. ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።

4. እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።

5. አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።

6. እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።

7. መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።

8. ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ ሁሉ ነው።

9. በቶሎ ወደ እኔ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤

10. ዴማስ ይህን ዓለም ወዶ፣ ትቶኝ ወደ ተሰሎንቄ ሄዶአልና። ቄርቂስ ወደ ገላትያ፣ ቲቶ ወደ ድልማጥያ ሄደዋል፤

11. ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው። ማርቆስ በአገልግሎቴ ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና።

12. ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኬዋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ጢሞቴዎስ 4