ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጢሞቴዎስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ክሕደት በመጨረሻዎቹ ቀናት

1. ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ።

2. ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣

3. ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣

4. ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና።

5. ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ።

6. እነርሱም በየቤቱ ሾልከው እየገቡ የኀጢአት ብዛት የተጫናቸውን፣ በተለያየ ክፉ ምኞት ውስጥ ገብተው የሚዋልሉ መንፈሰ ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ናቸው፤

7. እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ሁል ጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ አይችሉም።

8. ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት፣ እነዚህም አእምሮአቸው የጠፋባቸውና ከእምነት የተጣሉ ሰዎች ደግሞ እውነትን ይቃወማሉ።

9. ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም፤ ምክንያቱም የእነዚያ ሰዎች ሞኝነት እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ የእነዚህም ለሁሉ ግልጽ ይሆናል።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ዐደራ

10. አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዐላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና፣ ጽናቴን ሁሉ ታውቃለህ፤

11. ስደቴንና መከራዬን፣ በአንጾኪያና በኢቆንዮን፣ በልስጥራንም የደረሰብኝን ሁሉ፣ የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከእነዚህ ሁሉ አዳነኝ።

12. በርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።

13. ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።

14. አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤

15. ከሕፃንነትህም ጀምረህ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል።

16. ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤

17. ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።