ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ተሰሎንቄ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለጸሎት የቀረበ ጥያቄ

1. በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ ዘንድ እንደሆነው የጌታ ቃል በፍጥነት እንዲሠራጭና እንዲከበር ለእኛ ጸልዩልን፤

2. ደግሞም ሰው ሁሉ እምነት ያለው ስለማይሆን ከዐመፀኞችና ከክፉ ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን።

3. ጌታ ግን ታማኝ ነው፤ እርሱም ያበረታችኋል፤ ከክፉውም ይጠብቃችኋል።

4. እኛ ያዘዝናችሁን አሁን አደረጋችሁ፤ ወደ ፊትም እንደምታደርጉ በጌታ እንታመናለን።

5. ጌታ ልባችሁን ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ክርስቶስ ጽናት ይምራው።

ሥራ መፍታት እንደማይገባ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

6. ወንድሞች ሆይ፤ ሥራ ፈት ከሆነና ከእኛ በተቀበላችሁት ትምህርት መሠረት ከማይኖር ወንድም እንድትርቁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፤

7. የእኛን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደሚገባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና። ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤

8. ደግሞም የማንንም እንጀራ በነጻ አልበላንም፤ ነገር ግን ከእናንተ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እንደክምና እንሠራ ነበር፤

9. ይህን ያደረግነው ምሳሌነታችንን እንድትከተሉ ብለን እንጂ የሚያስፈልገንን ነገር ከእናንተ ለማግኘት ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም።

10. ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ፣ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብለን ይህን ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበርና።

11. ከእናንተ አንዳንዶች ሥራ ፈቶች እንደሆኑ ሰምተናል፤ እነርሱም ያለ ሥራ እየዞሩ በሰው ጒዳይ ጣልቃ የሚገቡ ናቸው።

12. እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተግተው ሥራቸውን እንዲሠሩና እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም።

13. እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፤ መልካም ሥራን ከመሥራት ከቶ አትታክቱ።

14. በዚህ መልእክት ላይ ላለው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ እንደዚህ ያለውን ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት፤ በሥራውም እንዲያፍር ከእርሱ ጋር አትተባበሩ።

15. ሆኖም እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቊጠሩት።

የመጨረሻ ሰላምታ

16. የሰላም ጌታ ራሱ በሁሉም ነገር ዘወትር ሰላም ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

17. ይህንን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁት እኔ ጳውሎስ ነኝ፤ የመልእክቶቼም ሁሉ መለያ ይህ ነው፤ አጻጻፌም እንደዚህ ነው።

18. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።