ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ለቅዱሳን ስለሚደረገው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግም።

2. ምክንያቱም ሌሎችን ለመርዳት ያላችሁን በጎ ፈቃድ ዐውቃለሁ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እናንተ በአካይያ የምትኖሩ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ለመቄዶንያ ሰዎች አፌን ሞልቼ ተናግሬአለሁ፤ ቅን ፍላጎታችሁም ብዙዎችን ለበጎ ሥራ አነሣሥቶአል።

3. እንግዲህ በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደ ተናገርሁት ተዘጋጅታችሁ እንድትገኙ ወንድሞችን ልኬአለሁ።

4. ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር መጥተው ሳትዘጋጁ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ያን ያህል በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን።

5. ስለዚህ ወንድሞች አስቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡና ከዚህ በፊት ለመስጠት ቃል የገባችሁትን ስጦታ አጠናቃችሁ እንድትጠብቋቸው፣ እነርሱን መለመን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቻለሁ፤ እንግዲህ በልግስና ለመስጠት ያሰባችሁት ነገር በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የተዘጋጀ ይሆናል።

በልግስና መስጠት

6. ይህን አስታውሱ፤ ጥቂት የዘራ ጥቂት ያጭዳል፤ ብዙ የዘራ ብዙ ያጭዳል።

7. እያንዳንዱ ሰው በቅሬታ ወይም በግዴታ ሳይሆን፣ በልቡ ያሰበውን ያህል ይስጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል።

8. ሁል ጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤

9. ይህም፣“በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል”ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

10. ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል።

11. ሁል ጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል።

12. ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጒድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው።

13. የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ስለ ታዘዛችሁና ለእነርሱም ሆነ ለሌሎች ስላሳያችሁት ልግስና ሰዎች ተፈትኖ ስላለፈው አገልግሎታችሁ እግዚአብሔርን ያከብራሉ፤

14. ስለ እናንተም በሚጸልዩበት ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ታላቅ ጸጋ የተነሣ ይናፍቋችኋል።

15. በቃላት ሊገለጥ ስለማይቻል ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።