ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 5:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።

2. እስከዚያው ግን የሰማዩን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን እንቃትታለን፤

3. በርግጥ ከለበስነው ራቊታችንን ሆነን አንገኝም።

4. በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም።

5. ለዚህ ዐላማ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ሊመጣ ላለው ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን መያዣ አድርጎ የሰጠንም እርሱ ነው።

6. ስለዚህ ሁል ጊዜ በመታመን እንኖራለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ እናውቃለን፤

7. ምክንያቱም የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም።

8. ከሥጋ ተለይተን ከጌታ ጋር መኖርን እንደምንመርጥ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ።

9. ስለዚህ በሥጋ ብንኖርም ወይም ከሥጋ ብንለይም ዐላማችን እርሱን ደስ ማሰኘት ነው።

10. ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል።

11. እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራለን። የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናችሁ ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

12. ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው።

13. ከአእምሮ ውጪ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው።

14. የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል።

15. በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 5