ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 4:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለዚህ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቈርጥም።

2. ነገር ግን ስውርና አሳፋሪ ነገሮችን ትተናል፤ አናታልልም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሐሰት ጋር አንቀላቅልም፤ ይልቁንም እውነትን በግልጽ እየተናገርን በሰው ሁሉ ኅሊና ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናቀርባለን።

3. ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ፣ የተከደነው ለሚጠፉት ነው።

4. የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሮአል።

5. እኛ የምንሰብከው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ መሆኑን እንጂ ራሳችንን አይደለምና፤ እኛም ራሳችን ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ አገልጋዮች ሆነናል።

6. በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶአልና።

7. ነገር ግን ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።

8. ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤

9. ብንሰ ደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም።

10. የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን።

11. የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁል ጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና።

12. እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ።

13. “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እኛም በዚያው የእምነት መንፈስ እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤

14. ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እኛንም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር አስነሥቶ ከእናንተ ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን።

15. ለብዙ ሰዎች እየደረሰ ያለው ጸጋ፣ ለእግዚአብሔር ክብር በምስጋና ላይ ምስጋናን እንዲጨምር ይህ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም ሆኖአል።

16. ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 4