ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎቹ ለእናንተ ወይም ከእናንተ የተጻፈ የምስጋና ደብዳቤ ያስፈልገን ይሆንን?

2. እናንተኮ ሰው ሁሉ የሚያውቃችሁና የሚያነባችሁ በልባችን ላይ የተጻፋችሁ ደብዳቤዎቻችን ናችሁ፤

3. እናንተ በቀለም ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ፣ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይሆን በሰው ልብ ጽላት ላይ የተጻፋችሁና በእኛ የተገለገላችሁ የክርስቶስ ግልጽ ደብዳቤ ናችሁ።

4. በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ይህን የመሰለ ነው፤

5. ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም።

6. እርሱም በፊደል ላይ ሳይሆን በመንፈስ ላይ የተመሠረተውን የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን፤ ምክንያቱም ፊደል ይገድላል፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።

7. እንግዲህ እስራኤላውያን ከፊቱ ክብር የተነሣ የሙሴን ፊት ትኵር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ፣ ያ ከጊዜ በኋላ የሚያልፈውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው የሞት አገልግሎት በክብር ከመጣ፣

8. ታዲያ፣ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ከዚያ የላቀ ክብር አይኖረውም?

9. ሰዎችን የሚኰንነው አገልግሎት የከበረ ከሆነ፣ የሚያጸድቀው አገልግሎት የቱን ያህል ይበልጥ የከበረ ይሆን!

10. ከዚህ በፊት ክቡር የነበረው የላቀ ክብር ካለው ጋር ሲወዳደር ክብር የሌለው ሆኖአል።

11. የሚያልፈው ያን ያህል ክብር ከነበረው፣ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም?

12. እንግዲህ ይህን የመሰለ ተስፋ ስላለን፣ በድፍረት እንናገራለን።

13. እስራኤላውያን የፊቱ ማንጸባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ፣ ፊቱን በጨርቅ እንደ ሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 3