ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 2:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማጋነን አይሁንብኝና ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው።

6. እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው።

7. ደግሞም ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።

8. ስለዚህ አሁንም የምትወዱት መሆናችሁን እንድትገልጹለት እለምናችኋለሁ።

9. የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር።

10. እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው።

11. ይህንንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የእርሱን ዕቅድ አንስተውምና።

12. የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤

13. ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ።

14. ነገር ግን በክርስቶስ ሁል ጊዜ በድል አድራጊነት እያዞረ ለሚመራን፣ የዕውቀቱንም መዐዛ በእኛ አማካይነት በየስፍራው ለሚገልጥ አምላክ ምስጋና ይሁን፤

15. ምክንያቱም በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዐዛ ነን።

16. ለሚጠፉት ወደ ሞት የሚወስድ የሞት ሽታ፣ ለሚድኑት ግን ወደ ሕይወት የሚወስድ የሕይወት ሽታ ነን፤ ታዲያ፣ ለዚህ ብቁ የሚሆን ማን ነው?

17. እኛኮ ትርፍ ለማግኘት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደተላኩ ሰዎች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት እንናገራለን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 2