ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 2:2-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. እኔ ባሳዝናችሁም እንኳ፣ ከእናንተው ካሳዘንኋችሁ በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን አለ?

3. ባለፈው ጊዜ እንደዚያ የጻፍሁላችሁ ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ በማለት ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የሁላችሁ ደስታ እንደሚሆን አምናለሁ።

4. እንደዚያ ስጽፍላችሁ በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፣ በብዙም እንባ ውስጥ ነበርሁ፤ ይህንንም ያደረግሁት ለእናንተ ያለኝን ጽኑ ፍቅር እንድታውቁ በማለት እንጂ፣ እናንተን ለማሳዘን አልነበረም።

5. ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማጋነን አይሁንብኝና ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው።

6. እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው።

7. ደግሞም ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።

8. ስለዚህ አሁንም የምትወዱት መሆናችሁን እንድትገልጹለት እለምናችኋለሁ።

9. የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር።

10. እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው።

11. ይህንንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የእርሱን ዕቅድ አንስተውምና።

12. የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በሄድሁ ጊዜ፣ ጌታ በር ከፍቶልኝ ነበር፤

13. ይሁን እንጂ ወንድሜን ቲቶን እዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ አላረፈም፤ ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 2