ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 11:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው።

5. እኔ ግን “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም የማንስ አይመስለኝም።

6. የንግግር ችሎታ ባይኖረኝም እንኳ፣ ዕውቀት ግን አለኝ፤ ይህንንም በሁሉ መንገድ በሚገባ ግልጽ አድር ገንላችኋል።

7. እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን ዝቅ አድርጌ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ ለእናንተ መስበኬ እንደ ኀጢአት ተቈጥሮብኝ ይሆን?

8. እናንተን ለማገልገል ስል ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ በመቀበሌ እነርሱን ዘርፌአቸዋለሁ።

9. ከእናንተም ጋር ሳለሁ አንዳች ባስፈለገኝ ጊዜ፣ ከመቄዶንያ የመጡ ወንድሞች የሚያስፈልገኝን ስለ ሰጡኝ ለማንም ሸክም አልሆንሁም። በእናንተ ላይ በምንም ነገር ሸክም እንዳልሆን ተጠንቅቄአለሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ።

10. የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ፣ በአካይያ አውራጃ ይህን ትምክሕቴን ማንም ሊገታው አይችልም።

11. ይህን የምለው ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነውን? እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል።

12. ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን በሥራቸው እየተመኩ ቀን የሚጠብቁትን ሰዎች ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደ ፊትም አደርጋለሁ።

13. እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው።

14. ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋው ጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 11