ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 11:21-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. እኛ ግን ለዚያ እጅግ ደካሞች መሆናችንን እያፈርሁ እናገራለሁ።ማንም በድፍረት በሚመካበት ነገር ሁሉ እኔም ደፍሬ መመካት እንደምችል እንደ ሞኝ እናገራለሁ።

22. እነርሱ ዕብራውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ እስራኤላውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ።

23. የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እንደ አበደ ሰው ልናገርና እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬያለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቤአለሁ።

24. አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል።

25. ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና ቀን በባሕር ላይ አድሬአለሁ፤

26. ብዙ ጊዜ በጒዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር።

27. ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በራቍትነት ተቈራምጃለሁ።

28. ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው።

29. ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን? በኀጢአት የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልቈጭምን?

30. መመካት ካለብኝ፣ ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች እመካለሁ።

31. ለዘላለም የተመሰገነው የጌታ የኢየሱስ አምላክና አባት እንደማልዋሽ ያውቃል።

32. ደማስቆ ሳለሁ ከንጉሥ አርስጦስዮስ በታች የሆነው ገዥ ሊያሲዘኝ ፈልጎ፣ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር።

33. ነገር ግን በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 11