ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 11:10-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. የክርስቶስ እውነት በውስጤ እስካለ ድረስ፣ በአካይያ አውራጃ ይህን ትምክሕቴን ማንም ሊገታው አይችልም።

11. ይህን የምለው ለምንድን ነው? ስለማልወዳችሁ ነውን? እንደምወዳችሁ እግዚአብሔር ያውቃል።

12. ከእኛ ጋር እኩል ለመሆን በሥራቸው እየተመኩ ቀን የሚጠብቁትን ሰዎች ምክንያት ለማሳጣት አሁን የማደርገውን ወደ ፊትም አደርጋለሁ።

13. እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት ለመምሰል ራሳቸውን የሚለዋውጡ፣ ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች ናቸው።

14. ይህም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋው ጣል።

15. እንግዲህ የእርሱ አገልጋዮች፣ የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለውጡ የሚያስገርም አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል።

16. እንደ ገና ይህን እላለሁ፤ ማንም ሰው እንደ ሞኝ አይቍጠረኝ፤ እናንተም የምትቈጥሩኝ ከሆነ እኔም በጥቂቱ እንድመካ እንደ ሞኝ ተቀበሉኝ።

17. እንደዚህ ልበ ሙሉ ሆኜ የምናገረው እንደ ሞኝ እንጂ እንደ ጌታ ፈቃድ አይደለም።

18. ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔም ደግሞ እመካለሁ።

19. እናንተም ብልሆች ስለ ሆናችሁ ሞኞችን በደስታ ትታገሣላችሁ፤

20. ማንም ተነሥቶ ባሪያ ቢያደርጋችሁ፣ ቢበዘብዛችሁ፣ ለጥቅሙ ሲል ቢጠጋችሁ፣ ቢንቀባረርባችሁ ወይም ፊታችሁን በጥፊ ቢመታችሁ ትታገሣላችሁ።

21. እኛ ግን ለዚያ እጅግ ደካሞች መሆናችንን እያፈርሁ እናገራለሁ።ማንም በድፍረት በሚመካበት ነገር ሁሉ እኔም ደፍሬ መመካት እንደምችል እንደ ሞኝ እናገራለሁ።

22. እነርሱ ዕብራውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ እስራኤላውያን ናቸውን? እኔም ነኝ፤ የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔም ነኝ።

23. የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እንደ አበደ ሰው ልናገርና እኔ እበልጣቸዋለሁ፤ ደግሞም ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬያለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት ተቃርቤአለሁ።

24. አይሁድ ለአርባ ጅራፍ አንድ የቀረው አምስት ጊዜ ገርፈውኛል።

25. ሦስት ጊዜ በዱላ ተደብድቤአለሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወግሬአለሁ፤ ሦስት ጊዜ የመርከብ አደጋ ደርሶብኛል፤ አንድ ሌሊትና ቀን በባሕር ላይ አድሬአለሁ፤

26. ብዙ ጊዜ በጒዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር።

27. ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በራቍትነት ተቈራምጃለሁ።

28. ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 11