ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ቆሮንቶስ 1:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ልታነቡት ወይም ልትረዱት የማትችሉትን ነገር አንጽፍላችሁም፤ ሁሉንም እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ።

14. እናንተ በእኛ እንደምትመኩ ሁሉ እኛም በእናንተ እንደምንመካ አሁን የተረዳችሁን በከፊል ቢሆንም፣ በጌታ ኢየሱስ ቀን ሁሉን ትረዳላችሁ።

15. በዚህ ርግጠኛ ስለ ነበርሁ በዕጥፍ እንድትጠቀሙ፣ በመጀመሪያ ልጐበኛችሁ ዐቅጄ ነበር።

16. ወደ መቄዶንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁና ከመቄዶንያም በእናንተ በኩል ተመልሼ ወደ ይሁዳ ስሄድ በጒዞዬ እንድትረዱኝ ዐቅጄ ነበር።

17. ይህን ሳቅድ በሚገባ ሳላስብ ያደረግሁት ይመስላችኋልን? ወይስ በዓለማዊ ልማድ አንዴ፣ “አዎን፣ አዎን” ወዲያው ደግሞ፣ “አይደለም፣ አይደለም” የምል ይመስላችኋልን?

18. እግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ሁሉ፣ ለእናንተ የምንናገረው ቃላችን፣ “አዎን” እና “አይደለም” ሊሆን አይችልም፤

19. ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው።

20. በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።

21. እንግዲህ፣ እኛንም እናንተንም በክርስቶስ ጸንተን እንድንቆም የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው፤ የቀባንም እርሱ ነው፤

22. የእርሱ ለመሆናችን ማኅተሙን ያተመብን ደግሞም ወደ ፊት ለምናገኘው ነገር የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው።

23. ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ ብዬ ነው፤ ይህ እውነት ካልሆነ እግዚአብሔር ይመስክርብኝ።

24. ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ቆሮንቶስ 1