ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 5:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንግዲህ ከእነርሱ ጋር እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤

2. በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤

3. እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን።

4. የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ።

5. ጐልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”

6. ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤

7. እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።

8. ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል።

9. በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።

10. በክርስቶስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።

11. ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።

12. እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በስልዋኖስ አማካይነት ይህንን አጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ።

13. ከእናንተ ጋር የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።

14. በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጴጥሮስ 5