ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 4:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ።

8. ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤

9. እርስ በርሳችሁ ያለ ማጒረምረም እንግድነት ተቀባበሉ።

10. እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል፤

11. ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው፤ ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

12. ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤

13. ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ።

14. ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ።

15. ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል፤

16. ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር፤

17. ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአልና። እንግዲህ ፍርድ የሚጀምረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን?

18. እንግዲህ፣“ጻድቅ የሚድነው በጭንቅ ከሆነ፣ዐመፀኛውና ኀጢአተኛው እንዴት ሊሆን ይሆን?”

19. ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጴጥሮስ 4