ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 3:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው፣ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።

8. በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩችና ትሑታን ሁኑ።

9. ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው።

10. ስለዚህ፣“ሕይወትን የሚወድ፣መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ምላሱን ከክፉ፣ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።

11. ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤

12. ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”

13. መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው?

14. ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ፤ አትታወኩም።”

15. ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤

16. በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ።

17. የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤

18. እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጴጥሮስ 3