ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 2:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

16. እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።

17. ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።

18. እናንተ አገልጋዮች ሆይ፤ ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ።

19. ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል።

20. ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብት ቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል።

21. የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።

22. “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።”

23. ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።

24. ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል።

25. ቀድሞ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጴጥሮስ 2