ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጴጥሮስ 2:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ፤

2. በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤

3. ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

4. በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣

5. እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ።

6. ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣በጽዮን አኖራለሁ፤በእርሱም የሚያምን፣ ከቶ አያፍርም።”

7. እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8. ደግሞም፣ “ሰዎችን የሚያሰናክል፣የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

9. እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ።

10. ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።

11. ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጴጥሮስ 2